Vision

Our Vision (ራዕያችን)

የኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤተክርስቲያን በቦልቲሞር አላማችን “ክርስቶስን በመምሰል ወደ እግዚአብሄር ፍጹም ሙላት ለመድረስ” ነው። ይህንን ራዕይ በህይወታችን ለመተርጎምና እውን ለማድረግ የሚያስችሉን አምስት አላማዎች አሉን። እውነተኛ አምልኮ ፤ እውነተኛ ህብረት ፤ እውነተኛ ደቀመዝሙርነት ፤ እውነተኛ አገልግሎትና እውነተኛ የወንጌል ስርጭት ክርስቶስን የምንመስልባቸው አላማዎቻችን ናቸው። ሰዎች በእነዚህ በአምስቱ አላማዎች እያደጉና እየበሰሉ ወደ ክርስቶስ አምሳያ ደርሰው በሚኖሩበት ህብረተሰብ (በቤታቸው ፤ በትምህርት ቤታቸው ፤ በስራቸው ፤ በጎረቤቶቻቸው ፤ በጓደኞቻቸው ፤ ወ.ዘ.ተ) ሆነ በአለም ዙሪያ ለክርስቶስ ለውጥ ማምጣት ሲችሉ ለማየት የቤተክርስቲያናችን ናፍቆት ነው።

ታዲያ እንዴት ነው ስዎች ከዕለት ወደ ዕለት ህይወታቸው ተለውጦና እውነተኛ የክርስቶስ ደቀመዝሙር ሆነው እንደዚህ አይነት ለውጥ አምጪዎች መሆን የሚችሉት?

በህይወታችን ውስጥ ፤ የመጀመሪያውን ለወጥ የሚጀምረው እግዚአብሄር እራሱ ነው። እግዚአብሄር በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል ሞት ከሱ ጋር ሲያስታርቀን ፤ ከድሮ ማንነታችን ተለውጠን አዲስ ፍጥረት እንድንሆን አስችሎናል። ይህን ፀጋ ወይንም ነጻ ስጦታ ስንቀበል አዲስ ፍጥረት ብቻ ሳይሆን የሆነው ፤ ሌሎች ወደ እግዚአብሄር መንግስት ገና ላልመጡ በአለም ላሉ ሰዎች ከእግዚአብሄር ጋር የምናስታርቅ አገልጋዮችም ጭምር ነው የሆንነው(2ቆሮ 5፡17-20)።

አንድ ሰው ክርስቶስን እንደ ግል አዳኙ ሲቀበል ፤ ያ ሰው ከእግዚአብሄር ጋር የሚያስደንቅና የማያቋርጥ ጉዞ ይጀምራል።በዚህ የጉዞ ወቅቱም ሰውዬው ከአዲስ አማኝነት ወደ ተሰጠ የክርስቶስ ደቀመዝሙርነት (ወይም የተሰጠ የክርስቶስ ተከታይና አገልጋይነት) ለመድረስ ከቀን ወደቀን እየተለወጠ ክርቶስን ወደመምሰል ያድጋል። ይህ የዕለት ከዕለት የህይወት መለወጥ ስራ ፤መንፈስ ቅዱስ በአማኙ ህይወት ውስጥ የሚሰራው የስራ ውጤት ነው።

የዕለት ከዕለት የህይወት ለወጥ በአማኙ ህይወት ውስጥ እንዲከሰት ከአማኙ የሚጠበቁበት ነገሮች አሉ(ፊሊ 2፡1-13)። በዕለት ከዕለት ኑሮአችን የመንፈስ ቅዱስን ምሪት መለየትና ማወቅ እንዲሁም የመንፈስ ቅዱስን ምሪት ሙሉ በሙሉ በመታዘዝ ለማስተናገድ የተዘጋጀን መሆን አለብን። ዕለት በዕለት በመንፈስ ቅዱስ ስንሞላና ለሱ ፈቃድ ስንታዘዝ ብቻ ነው ክርስቶስን መከተል ፤ ለክርስቶስ ጌትነት መገዛት ፤ ክርስቶስን መምሰል ፤ የተሰጠን የክርስቶስ ተከታዮች ወይንም የክርስቶስ ደቀመዛሙርት መሆን የምንችለው።

በኢትዮጱያ ወንጌላዊት ቤተክርስቲያን የመንፈስ ቅዱስን ምሪት ለማወቅ ፤ የኛን ፈቃድ ለሱ ፈቃድ ለማስገዛት ፤ እንዲሁም ለሱ ምሪት በታዛዥነት ራስን ለመስጠት መንፈሳዊ ሥነ-ስርዓት (ዲሲፕሊን) እንደሚያስፈልግ እናምናለን። መንፈሳዊ ዲሲፕሊን ፤ ክርስቶስን እየመሰልን ፤ የተሰጠን የክርስቶስ ደቀመዛሙርት እንድንሆን የሚያደርገን ዋነኛ መሳሪያ እንደሆነ እናምናለን። ስለዚህም የቤተክርስቲያናችንን አማኞች መንፈሳዊ ዲሲፕሊንን በህይወታቸው እንዲለማመዱና እንዲያዳብሩ እጅግ በጣም እናበረታታቸዋለን።

Reaching the fullness of God by becoming Christ Like