Steps Of Commitment (የመሰጠት ደረጃዎች)

የመሰጠት ደረጃዎች:
የመሰጠት ደረጃዎች ሰዎች እንደ እግዚአብሄር ቃል በህይወታቸው ምን ደረጃ ላይ እንዳሉ የሚያሳይ ነው። ለአማኞች ራሳቸውን በማየት በየት ደረጃ ላይ እንደሚገኙና አሁን ካሉበት ደረጃ ወዴት መሄድ እንዳለባቸው የሚመራ ነው። ከዚህም በላይ ከአንዱ ደረጃ ወደሚቀጥለው ደረጃ ለማደግ አማኙ የትኛውን ትምህርት መውሰድ እንዳለበት ይገልጻል። የእያንዳንዱ ደረጃ ገለጻ እንደሚከተለው ነው ፦
1) ህብረተሰብ - በዚህ ደረጃ የሚገኙት ሰዎች ቤተክርስቲያናችን ልትደርሳቸው የሚገቡ ሰዎች ናቸው። በቦልቲሞር የምትገኘው የኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤተክርስቲያን በዚህ ረገድ ያላት ራዕይ በቀደምት በቦልቲሞርና በአካባቢዋ የሚገኙትን ኢትዮጵያውያንንና ኤርትራዊያንን ለመድረስ ከዛም እግዚአብሄር በሩን በከፈተላት መጠን ደግሞ በአካባቢዋ የሚኖሩትን የአገሩን ሰዎች መድረስ ነው። ከዚህም ባሻገር ፤ ወንጌልን በተለያዩ አገሮች ለማሰራጨትና ሚሲዮናውያንን ለመላክ ባላት ራዕይ መሰረት በሌሎችም አገር በዚች ቤተክርስቲያን አማካኝነት ሊደረሱ ያሉ ሰዎች በዚህ ደረጃ ውስጥ ይጠቃለላሉ። በዚህ ደረጃ ለሚገኙ ሰዎች የቤተክርስቲያን አላማ እውነተኛ ወንጌል ስርጭትን ማካሄድ ነው።
2) የተጠራ ህዝብ - በዚህ ደረጃ የሚገኙ ሰዎች ወደ ቤተክርስቲያናችን ህብረት መምጣት የጀመሩ ነገር ግን ገና የቤተክርስቲያን አባል ያልሆኑትን ሰዎች ያጠቃልላል። እነዚህ ሰዎች ክርስቶስን እንደ ግል አዳኛቸው መቀበላቸው ፤ የውሃ ጥምቀት መውሰዳቸው ፤ የአባልነት ትምህርት መውሰዳቸው ፤ የአባልነት ኪዳን ቅጽ ሞልተው መፈረማቸው ተረጋግጦ ሲያበቃ በቤተክርስቲያን ጉባኤ ፊት ተጸልዮላቸው የቤተክርስቲያኒቱ አባል ይሆናሉ። በዚህ ደረጃ ለሚገኙ ሰዎች የቤተክርስቲያን አላማ ሰዎቹን ወደ እውነተኛ ህብረት ማዋሃድ የሆናል። ለዚህም እንዲያግዝ ቤተክርስቲያን ያዘጋጀችውን “የአባልነት ትምህርት” በዚህ ደረጃ ያሉ ሰዎች እንዲወስዱ ታደፋፍራለች።
3) የእግዚአብሄር ቤተሰብ - በዚህ ደረጃ የሚገኙ ሰዎች ክርስቶስን እንደ ግል አዳኛቸው የተቀበሉ ፤ የውሃ ጥምቀት የወሰዱ ፤ የአባልነት ትምህርት ወስደው የጨረሱ ፤ የአባልነት ኪዳን ቅጽ ሞልተው የፈረሙና በጉባኤ ተጸልዮላቸው የቤተክርስቲያን አባል የሆኑ ሰዎችን ያጠቃልላል። በዚህ ደረጃ ያሉ ሰዎች የቤተክርስቲያንን ራዕይ ተረድተው ወደዛ ራዕይ ለመድረስ ከቀን ወደ ቀን ትጋት እንዲያሳዩ ይጠበቅባቸዋል። በተጨማሪም እዚህ ደረጃ ላይ ያሉ ሰዎች በመንፈሳዊ ህይወታቸው ዕለት ከዕለት እያደጉ ወደ ክርስቶስ አምሳያ እንዲያድጉ ይጠበቅባቸዋል። በዚህ ደረጃ ለሚገኙ ሰዎች የቤተክርስቲያን አላማ ሰዎቹን ወደ እውነተኛ ደቀመዝሙርነት ማሳደግ ይሆናል። ለዚህም እንዲያግዝ ቤተክርስቲያን ያዘጋጀችውን “የደቀመዝሙርነት ትምህርት” በዚህ ደረጃ ያሉ ሰዎች እንዲወስዱ ታደፋፍራለች።
4) የተሰጡ - በዚህ ደረጃ የሚገኙ ሰዎች የደቀመዝሙርነትን ትምህርት ወስደው ፤ የደቀመዝሙርንተ ኪዳን ቅጽ ሞልተውና ፈርመው ፤ በዕለት ከዕለት ኑሮአቸው በደቀመዝሙርነት ትምህርት የተማሩዋቸውንና ወደ መንፈሳዊ ብስለት የሚያሳድጉዋቸውን መንፈሳዊ ልማዶች በታማኝነት የሚለማመዱ ሰዎችን ያጠቃልላል። በዚህ ደረጃ ለሚገኙ ሰዎች የቤተክርስቲያን አላማ ሰዎቹ እውነተኛ አገልጋይ እንዲሆኑ ማሳደግ ነው። ለዚህም እንዲያግዝ ቤተክርስቲያን ያዘጋጀችውን “የአገልግሎት ስልጠና ትምህርት” በዚህ ደረጃ ያሉ ሰዎች እንዲወስዱ ታደፋፍራለች።
5) አዕማድ - በዚህ ደረጃ የሚገኙ ሰዎች የአገልግሎት ስልጠናን ትምህርት አጠናቀው ፤ ከእግዚአብሄር የተቀበሉትን ስጦታና ጥሪ ለይተው ፤ በቤተክርስቲያን ውስጥ ጌታ በከፈተላቸው በር ተሰማርተው ፤ የእግዚአብሄርን ሃሳብና የቤተክርስቲያኒቱን ራዕይ የሚያገለግሉ ፤ ለጌታ ራሳቸውን አሳልፈው የሰጡና ፤ በመንፈሳዊ ብስለት የበሰሉ ሰዎችን ያጠቃልላል። በዚህ ደረጃ የሚገኙ ሰዎች ከላይ በተጠቀሱትን የመሰጠት ደረጃዎች ደረጃ በደረጃ አልፈው ሲጨሩሱና ወደዚህ መጨረሻ ደረጃ ላይ ሲደርሱ ቤተክርስቲያን ተመልሰው ወደ መጀመሪያው የመሰጠት ደረጃዎች እንዲመለሱ ታደርጋለች። በዚህ ጊዜ ግን ወደ “ህብረተሰብ” ደረጃ የሚመለሱት የወንጌል ባለአደራ ሆነው ነው። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንዲሁም ሐዋሪያው ጳውሎስ ፤ ራሳቸውን ዝቅ አድርገው ፤ አካባቢያቸውን መስለው ፤ የምስራቹን ቃል በጥፋት ላይ ላሉና በእግዚአብሄር አምሳል ለተፈጠሩ ሰዎች በፍቅር ለማድረስ ራሳቸውን አሳልፈው እንደሰጡ በዚህ ደረጃ ያሉ ሰዎችም የነሱን ፈለግ ተከትለው ለእውነተኛ ወንጌል ስርጭት ራሳቸውን እንዲሰጡ ይጠበቅባቸዋል። በዚህ ደረጃ ለሚገኙ ሰዎች የቤተክርስቲያን አላማ ሰዎቹን እውነተኛ አምላኪዎች እንዲሆኑ ማሳደግ ነው። ለዚህም እንዲያግዝ ቤተክርስቲያን ያዘጋጀችውን “የወንጌል ስርጭት ስልጠና ትምህርት” በዚህ ደረጃ ያሉ ሰዎች እንዲወስዱ ታደፋፍራለች።

Steps of Commitment